Fana: At a Speed of Life!

የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች ተግባር የህዝቦችን አብሮነት ማጠናከሩ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች ተግባር የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት እያጠናከረ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በመዟዟር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን እያከናወኑ ያሉ የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች ቡድን በሐረሪ ክልል በመገኘት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አከናውነዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ሙና አህመድ እንደተናገሩት÷ ባለፉት ዓመታት በወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ በመትከል፣ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት በማደስ፣ ደም በመለገስና በሌሎች በ14 ዓይነት ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በጎ ፈቃደኞቹ በየክልሉ በጎ ተግባራት ሲያከናውኑ የየክልሉን ባህል፣ ወግ እና እሴቶችን እንዲያውቁ ማስቻሉንም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ወጣቶች እርስ በርስ እንዲተዋወቁና ማህበራዊ ትስስራቸው እንዲዳብር እድል መፍጠሩን ነው የገለጹት፡፡

ወጣቶች ዝቅ ብለው ለሀገራቸውና ለወገናቸው እንዲያገለግሉና የስራ ባህልን እንዲያዳብሩ ከማስቻሉ በተጨማሪ አብሮነትና አንድነትን አጠናክሯል ሲሉ መጥቀሳቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.