የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡
በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በሚገኘው የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሚካሄደው ጉባዔ የምክር ቤቱ አባላት፣ አስፈጻሚ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በጉባዔው÷ የአዲስ አበባ ከተማ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሏል፡፡
እንዲሁም የአስተዳደሩ የዋና ኦዲተር የ2016 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት ላይ እንደሚወያይና የ2017 በጀት ረቂቅ አዋጅም እንደሚያጸድቅ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አደረጃጀት አሠራር እና የአባላት ሥነ-ምግባር ማሻሻያ ረቂቅ ደንብ ላይም ጉባዔው ከተወያየ በኋላ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡
ከንቲባ አዳነች የቤት ልማትና ማስተላለፍን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት÷ 17 ሺህ 635 ቤቶች በመንግስት በጀትና አስተባባሪነት ተገንብተው ለልማት ተነሺዎችና ሌሎች ተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን ገልጸዋል፡፡
በጋራ መኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበርም 4 ሺህ 940 ነዋሪዎች በ60 ማኅበራት መደራጀታቸውን እና ከእነዚህ መካከል 54 ማኅበራት ቦታ ተረክበው ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በሪል ስቴት አልሚዎች ደግሞ 71 ሺህ 12 ቤቶች መገንባታቸውን ገልጸው÷ በ2016 በጀት ዓመት በመንግስት አስተባባሪነትና በግሉ ሴክተር 88 ሺህ 633 ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ቀርበዋል ብለዋል፡፡
በቀጣይም 120 ሺህ ቤቶች እንደሚገነቡ እና ከእነዚህ መካከል የ99 ሺህ 113 ቤቶችን ግንባታ ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡
እንዲሁም የ65 ሺህ 817 ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ነው የገለጹት፡፡