Fana: At a Speed of Life!

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በ2016 በጀት ዓመት ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሐሚድ ኪኒሶ፤ በቀን በአማካይ ከ6 ሺህ በላይ ተገልጋዮች ካለቀጠሮ እየተስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች 919 ሺህ 941 ጉዳዮችን ማስተናገድ መቻሉን ገልጸው፤ 726 ሺህ 535 ጉዳዮች በኦንላይን መሰጠታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የመኪና ሽያጭ፣ የባንክ ብድር ውል፣ ውክልና፣ የንግድ ማኅበራት መዝገባና ቃለ ጉባኤ መያዝ፣ ቃለ መሃላ፣ ከጋብቻ በፊት ያለ ንብረት ሥምምነት፣ የተረጋገጡ ዶክመቶችን ለባለመብቶች መስጠት አብዛኛው የተቋሙ ገቢ የተገኘባቸው አገልግሎቶች መሆናቸውን አመላክተዋል።

ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰጠውን አገልግሎት እያዘመነ ወረፋ አልባ አገልግሎት በመስጠቱ እንዲሁም ፍትኃዊነትንና ሁሉን አቀፍነትን ከማረጋገጥ አንጻር ሰፊ ሥራ መሥራቱ ለገቢው መጨመር ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም ለአቅመ ደካማች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ በህክምና ሆስፒታል ውስጥ ለተኙ ህሙማን፣ ለነፍሰ-ጡሮችና ለሚያጠቡ እናቶች ያሉበት ሥፍራ ድረስ በመሄድ አገልግሎት የሚሰጥበት አሰራን ተግባራዊ መደረጉን ለገቢው መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉንም አንስተዋል።

ተገልጋዮች የሚበዙባቸው ቅርንጫፎች ምሳ ሰዓትን ጨምሮ ከሰኞ እስከ አርብ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1፡00 አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.