Fana: At a Speed of Life!

በተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት 35 ሺህ 600 ዜጎች እየተመገቡ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ21 የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት 35 ሺህ 600 ዜጎች እየተመገቡ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ከንቲባዋ ሰው ተኮር እና በጎ ፍቃድ ሥራዎችን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት፤ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ኅብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ ማጋራት መቻሉን ተናግረዋል።

በሰው ተኮር እና በጎ ፈቃድ ሥራችን በ11 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ለመስጠት ታቅዶ በ12 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የበጎ ፈቃድ ተግባራት ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

በ21 የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላትም 35 ሺህ 600 ዜጎች እየተመገቡ ይገኛሉ ነው ያሉት ከንቲባዋ፡፡

በመዲናዋ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሥራ ዕድል እና በመንግስት የድጋፍ ማዕቀፎች ዙሪያ ከ369 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ግንዛቤ በመፍጠር በሕይወት ክህሎት፣ በሥራ ፈጠራና በንግድ ክህሎት የአመለካከት ግንባታ ሥልጠናዎች መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።

በቂ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ከመገንባት አንጻር በ2016 በጀት ዓመት 43 ማዘወተሪያ ስፍራዎችን በማልማት በመዲናዋ ያለውን የማዘውተሪያ ስፍራ ወደ 1 ሺህ 241 ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

13 የመደመር ትውልድ የህፃናትና የወጣቶች መጫወቻ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረግ እንደተቻለ መግለጻቸውንም የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.