የሽብር ተግባር በመፈጸም፣ ማነሳሳት፣ ድጋፍ ማድረግና መረጃ ማቀበል የተጠረጠሩ 7 ግለሰቦች በሽብር ወንጀል ተከሰሱ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ተግባር በመፈጸም፣ ማነሳሳት፣ ድጋፍ ማድረግ እና መረጃ ማቀበል ወንጀል የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦች በሽብር ወንጀል ተከሰሱ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የህገ መንግስትና በህገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ጉዳዮችን የሚመለከተው ወንጀል ችሎት በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የፀረ ሰላም ቡድን ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት በማድረግ የሽብር ተግባር መፈጸም፣ የሎጂስቲክ ድጋፍ ማድረግ፣ መረጃ ማቀበልና ለሽብር ተግባር ማነሳሳት በሚሉ በወንጀል ተሳትፎ የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦች ላይ በዐቃቤ ሕግ የተመሰረተውን የሽብር ወንጀል ክስ ተመልክቷል።
የፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ዘነበ ሽታ፣ አማንኤል ሳህልዬ፣ ፌቨን ዘሪሁን፣ ብስራት ካሳዬ፣ ገነት አራጌ፣ ሲሳይ ወርቁ፣ ያሲን ሞሄ በተባሉ ሰባት ግለሰቦች ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ዛሬ የሽብር ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የምርመራ ማጣሪያ ሲከናወንባቸው መቆየታቸው ይታወሳል።
በቀረበው አንደኛ ክስ ዐቃቤ ሕግ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ እንዳመላከተው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ፣ አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 38 እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በ2015 እና በ2016 ዓ.ም በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የፀረ ሰላም ቡድን ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት በማድረግ ገንዘብ በማሰባሰብ፣ የጦር መሳሪያ በመግዛት ድጋፍ በማድረግ፣ የጥፋት ተዕልኮ ተቀብሎ ንፁሃን እና የፀጥታ አካላት ላይ ጥቃት መፈጸምና ማስፈጸም የሚል የወንጀል የተሳትፎ ተግባር በዝርዝር ጠቅሷል።
በዚህም ተፈጸመ በተባለ ጥቃት 50 ሰዎች እንደተገደሉ፣ 40 ሰዎች ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ 82 ሰዎች እንደታገቱ እና 1 ቢሊየን 634 ሚሊየን 596 ሺህ 214 ብር የሚገመት ንብረት መዘረፉንና መውደሙን ጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተካፋይ በመሆን የሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በሁለተኛ ክስ ደግሞ ከ3ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ በቀረበው ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ፣ አንቀጽ 35 እና አንቀጽ 38 እንዲሁም የሽብር አዋጁን አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የፀረ ሰላም አባላት መመልመል፣ የሎጂስቲክ ድጋፍ ማድረግ፣ የሽብር አላማን ለማሳካት የሚያስችል ሰነዶችን ማዘጋጀት፣ የሽብር ተግባር እንዲፈጸም ድጋፍ ማድረግና መረጃ ማቀበል የሚሉ ተሳትፎዎች ተጠቅሶ በዝርዝር ቀርቧል።
በ3ኛው ክስ ላይ በ6ኛ እና በ7ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን፤ ይህም የሽብር አዋጁን አንቀጽ 10 ንዑስ 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በ2016 ዓ.ም የፀረ ሰላም ቡድን በህዝብና በመንግስት ላይ የሽብር ተግባር እንዲፈጽም የሚያነሳሱ መልክቶችን ያያዙ ጽሁፎችንና ምስሎችን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች በመለጠፍ እና በማጋራት ተግባር ተሳትፈዋል በማለት የሽብር ድርጊት እንዲፈጸም ማነሳሳት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ዝርዝር ክስ ችሎት ቀርበው እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ችሎቱ ማንነታቸውን በማረጋገጥ በቀረበባቸው ክስ ላይ በዋስትና ላይ የግራ ቀኝ ክርክር ለመመልከት ፍርድ ቤቱ በይደር ለነገ ከሰዓት በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ