ከኮምቦልቻ ባህር ዳር ቀጥታ በረራ ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኮምቦልቻ ወደ ባህር ዳር ከተማ ቀጥታ በረራ ሊጀመር መሆኑን አየር መንገዱ አስታውቋል።
በአየር መንገዱ የኮምቦልቻ ኤርፖርት ኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ሰለሞን አበበ እንደገለጹት÷ ከከምቦልቻ ወደ ባህር ዳር እና ከባህር ዳር ወደ ኮምቦልቻ የነበረው በረራ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡
አሁን መንገደኞች በተደጋጋሚ በረራው ዳግም እንዲጀመር በመጠየቃቸው አየር መንገዱ ከሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በየቀኑ በረራውን ዳግም እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡
በረራው መጀመሩ ከኮምቦልቻ ወደ ባህር ዳር ለመሄድና ከባህር ዳር ወደ ኮምቦልቻ ለመምጣት በአዲስ አበባ ይደረግ የነበረውን ጉዞ እንደሚያስቀር በመግለጽ ይህም የተገልጋዮችን እንግልትና ተጨማሪ ወጭ እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡
ተገልጋዮች ከሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ቀጥታ ከኮምቦልቻ -ባህር ዳርና ከባህር ዳር-ኮምቦልቻ መጓዝ እንደሚችሉ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኮምቦልቻ ኤርፖርት ወደ አዲስ አበባ በቀን 6 መደበኛ በረራ ሲኖረው÷ እንደ አስፈላጊነቱ ከ6 በላይ በረራ እንደሚያደርግም ለማወቅ ተችሏል፡፡