Fana: At a Speed of Life!

በክልሉ ከ11 ሺህ በላይ የታጠቁ ሃይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ማህበረሰቡን ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ከ11 ሺህ በላይ የታጠቁ ሃይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ማህበረሰቡን መቀላቀላቸውን የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል ም/ቤት የሕግ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን የአሥፈጻሚ አካላትን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

በም/ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ደሳለኝ ጣሰው÷ በዓመቱ የጸጥታ ችግሩ መደበኛ ዕቅዶችን ለመፈጸም እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል።

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ክልሉን ዘርፈ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለው ጠቁመው÷የተፈጠረው ችግር በአንድ ጊዜ የተነሳ ሳይሆን በብዙ ውጫዊና ውስጣዊ ግፊቶች የተነሳ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ከቆየው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ባለፈ በሱዳን የተፈጠረው ጦርነት በርካታ ስደተኞች ወደ ክልሉ እንዲገቡ ማድረጉን እና ጫና እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

በአጎራባች ክልሎች የአብሮነት እና የወንድማማችነት አቅም እንዲዳብር ዕቅድ ይዘው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አስታውሰዋል።

የክልሉ የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉን የተናገሩት ሃላፊው÷አሁንም የክልሉን ሰላም የሚያውክ ግጭት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

ከ11 ሺህ በላይ የታጠቁ ሃይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መግባታቸውን ሃላፊው መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ ወገኖች የተሃድሶ ሥልጠና እየተሰጣቸው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውንም አስታውቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.