Fana: At a Speed of Life!

በ76 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የተገነባው የፌዴራል ፖሊስ አቪዬሽን መኖሪያ ካምፕ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ76 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አቪዬሽን ፖሊስ መምሪያ መኖሪያ ካምፕ በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡

የመኖሪያ ካምፑ ግንባታ ሙሉ ወጪ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደተሸፈነ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት÷የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ ለደረሰበት ስኬት የፌዴራል ፖሊስ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፌዴራል ፖሊስ አገልግሎትን ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው÷ዛሬ የተመረቀው የፖሊስ መኖሪያ ካምፕ የዚህ ድጋፍ አካል ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው÷የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ለአቪዬሽን ኢንዱስትሪው፣ ለአየር መንገዱና ለመንገደኞች ሰላምና ደህንነት ዘብ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡

አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም በክልል አየር መንገዶች የጸጥታና ደህንነት ሥራ ለሚያከናውኑ የሠራዊቱ አመራርና አባላት መኖሪያ ቤት መገንባቱን አስታውሰዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በ76 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ ባለሁለት ወለል ሕንጻ አስግንበቶ ማስረከቡን ነው የገለጹት፡፡

ሕንጻው በውስጡ መኖሪያ ክፍሎች፣ ቢሮዎች፣ የመዝናኛና መመገቢያ አዳራሾች እንዲሁም ጅምናዚዬም ያካተተ  መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.