በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመዲናዋ ወንጀልን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል- የአዲስ አበባ ፖሊስ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመዲናዋ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ገለጹ።
ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው÷ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ2016 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኅን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መከላከል፣ ሰላምና ደኅንትን የማስጠበቅ ተቋማዊ አቅምን ማጎልበት የሚያስችል ስኬታማ የለውጥ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
በለውጥ እርምጃዎቹም የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ እንዲሁም ኃይማኖታዊና ህዝባዊ የአደባባይ በዓላትንና ስፖርታዊ ክዋኔዎችን በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ የተቻለበት ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ አንስተዋል።
በወንጀል መከላከል ረገድ በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በስርቆትና ተያያዥ ከቀላል እስከ ከባድ የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል።
በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ወንጀል የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ከ13 ሺህ በላይ መዛግብት ተደራጅተው ለዓቃቤ ሕግ መላካቸውን አንስተዋል።
አደንዛዥ ዕፆችን ሲጠቀሙና ሲያስጠቅሙ እንዲሁም ቁማር ሲያጫውቱ የተገኙ አካላት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተደርጓል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የተለያየ አይነት የጦር መሳሪያና ተተኳሾችን፣ የመገናኛ ራዲዮ፣ ሕገ-ወጥና ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ጨምሮ በርካታ የአገር ውስጥና የሌሎች ሀገራት ገንዘብ ኖቶች መያዛቸውን አስረድተዋል።
የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት ለማናጋት ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ በተወሰደው እርምጃም በሀገር ላይ ሊደርስ የነበረን ከፍተኛ አደጋ መቀልበስ የተቻለበት ስኬታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ሚሊኒዬም አዳራሽ አካባቢ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 38 የፅንፈኛው ቡድን አባላትን ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ማለታውን ኢዜአ ዘግቧል፡፤
በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ባልሆኑ የቡድኑ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ልዩ ልዩ ኤግዚቢቶች መያዛቸውንም አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ በተወሰዱ ፖሊሳዊ እርምጃዎች 7 ሺህ 405 ከባድ እና ከ26 ሺህ በላይ መካከለኛ ወንጀል የፈጸሙ አካላት እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ገልጸዋል።
ፖሊስ በበጀት ዓመቱ በነበረው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ስራም የህዝብ የዕለት ከዕለት እንቅሰቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ከባድ ወንጀልን በ31 በመቶ መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው የዲሲፕሊን ጥሰት የፈጸሙ በርካታ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ላይ ከቀላል እስከ ከባድ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ፖሊስ በተደራጀ መንገድ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እና የሽብር ተግባራትን የመከላከልና የማክሸፍ ተልዕኮውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።