የሞሮኮ ምክትል ኢታማዦር ሹም የኮማንዶ አየር ወለድ ትምህርት ቤትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞሮኮ ምክትል ኢታማዦር ሹም ሜጀር ጀኔራል አዚዝ እድሪስ የተመራ ልዑክ በኮማንዶ አየር ወለድ ዕዝ የአየር ወለድ ትምህርት ቤትን ጎብኝቷል።
በማዕከሉ የአመራር ትምህርት ቤት አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ሰማኸኝ ሃይሉ÷ስለ አየር ወለድ ትምህርት ቤቱ ለልዑካን ቡድኑ አባላት አብራርተዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ ያሉትን ልዩ ልዩ የሥልጠና ክፍሎችን አቅም በመጠቀም በተቋሙ ውስጥ በርካታ አቅሞችን መፍጠር እደቻለ አንስተዋል፡፡
በሀገር ውስጥ እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት የሰላም ማስከበር ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ያለ ሠራዊት መገንባት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
ሜ/ጀ አዚዝ እድሪስ በበኩላቸዉ÷ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀደምት አየር ወለድ ሠራዊትን ያቋቋመች ሀገር ናት ፤ሠራዊቷም ረጅም ታሪክ ያለው የድል ሰራዊት መሆኑም ይታወቃል ፤እኛም ከዚህ ብዙ ልምድና ተሞክሮን አግኝተናል ብለዋል፡፡
“ጥሩ የልምድ ልውውጥ በማድረግ የኮማንዶ፣ የልዩ ሃይልና የአየር ወለድ አቅሞቻችንን ለማሳደግ በጋራ እንሰራለን ፤የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠንካራ ነው” ሲሉ መናገራቸውንም ከመከላከያ ሰራዊት የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ÷ያሉትን ልምድና ተሞክሮዎች በመለዋወጥ የአሰልጣኞችን እና የአመራሮችን አቅም ለመገንባትና ለማሳደግ በጋር መስራት ይገባናል ብለዋል፡፡
ጀነራል መኮንኖቹ በጋራ በመሆን በቢሾፍቱ የአየር ወለድ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን ማኖራቸው ተጠቁሟል፡፡