90 ሺህ 175 ቶን ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 90 ሺህ 175 ቶን ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፅዳት ኤጀንሲ ገለጸ ፡፡
የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሙላት ተገኝ እንዳሉ÷ ከተማዋን ውብ፣ ጽዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ፡፡
የከተማዋን ደረጃ በሚመጥን ልክ ውበትና ፅዳቷን ለማስጠበቅ በመዲናዋ የሚገኙ 119 ወረዳዎችና 4 ሺህ 992 ብሎኮችን ተደራሽ ያደረገ የፅዳት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡
ህብረተሰቡ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓት ግንዛቤ እንዲኖረው 2 ሺህ ባለሙያዎች ተመደብው ብሎክን ማዕከል በማድረግ ቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
ከ 6 ሺህ በላይ አባላት የያዙ የሽርክና ማህበራት በሳምንት ሁለት ጊዜ በቋሚነት ከየቤቱና ከየብሎኩ ቆሻሻ እያነሱ መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሩ አክለዋል ፡፡
በከተማዋ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩትን የኮሪደር ልማቶች ፅዳት ለመጠበቅ በየ 100 ሜትር የቆሻሻ መጣያዎች መገንባታቸውን ጠቁመዋል ፡፡
ማህበራቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 90 ሺ 175 ቶን ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘታቸውንም ለኢዜአ ገልጸዋል ፡፡