ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመቐለ ከተማ ዙሪያ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኖሩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከክልሎችና ከከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመቐለ ከተማ ዙሪያ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
በመቐለ ከተማ ዙሪያ የተካሄደው ችግኝ ተከላ ወጣቶቹ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚያከናውኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ-ግብር አካል መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወጣቶቹ ከሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ችግኝ በመትከል፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ እና አረጋውያንን በመርዳት በጎ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የደም ልገሳ፣ የጽዳትና መሰል የበጎ አገልግሎት ሥራዎችን ማከናወናቸውንም በሚኒስቴሩ የወጣቶች የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አስተባባሪ እንደገና ፍቃዱ ገልፀዋል።
የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቱ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ ዐሻራውን ከማኖር ባለፈ አብሮነትና አንድነቱን የማጠናከር ዓላማ አለው ብለዋል፡፡