Fana: At a Speed of Life!

ምርት ገበያው በህዳር ወር 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች አገበያየ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በህዳር ወር 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸውን 60 ሺህ 825 ቶን ምርቶች ማገበያየቱን አስታወቀ።

ምርት ገበያው ለጣቢያችን በላከው መግለጫ በህዳር ወር ከተገበያዩት ምርቶች ውስጥ ቡና 36 በመቶ የግብይት መጠንና 50 በመቶ የግብይት ዋጋ በማስመዝገብ ቀዳሚ መሆኑን አስታውቋል።

የወሩ የቡና ግብይት ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸርም በመጠን የ3 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያለው።

ከዚህ ባለፈም በወሩ ለገበያ የቀረበ 5 ሺህ 428 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ127 ሚሊየን ብር ተገበያይቷል።

በተጨማሪም 1 ሺህ 83 ቶን አኩሪ አተር በ16 ነጥብ 18 ሚሊየን ብር ሲገበያይ፥ ከዚህ ውስጥ የጎጃም አኩሪ አተር 67 በመቶ በመጠን እንዲሁም 71 በመቶ በዋጋ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል።

በተያያዘም ኑግ በምርት ገበያው 10ኛ ምርት ሆኖ ከታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት መቀላቀሉን ገልጿል።

አዲስ አበባ ሳሪስ፣ ቡሬ፣ ነቀምት፣ ጎንደር፣ ኮምቦልቻ፣ አሶሳና ፓዊ ከተሞች የኑግ መረከቢያ ቅርንጫፎች ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.