ግብፅ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላት ተቃውሞ ፖለቲካዊ እንጅ ሳይንሳዊ ምክንያት የለውም – ግብፃዊ ምሁር
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅ በህዳሴ ግድብ ላይ የምታነሳው ተቃውሞ ፖለቲካዊ እንጂ ሳይንሳዊ ምክንያት እንደሌለው ግብፃዊው የስነ ምድር ምሁር ፍሩዝ አልባዝ ተናገሩ።
ምሁሩ ከኤም ቢ ሲ ዓረብኛ ዩ ቲዩብ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት “የግድቡ ውሃ ሙሌት ግብፅን ለውሃ ዕጥረት ይዳርጋል” ተብሎ የሚወራው የግብጽ ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙሃኗ ፕሮፓጋንዳ እንጅ እውነታን የተከተለ አይደለም።
ምሁሩ አክለውም ግድቡ የውሃው ፍሰት ላይ የሚያመጣው ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ እንደሌለውም አውስተዋል።
በሌላ በኩል የህዳሴ ግድብ ግንባታ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ግድቡ ብዙ ጥናት ተደርጎበትና በዓለም አቀፍ ኩባንያ እየተገነባ በመሆኑ የደህንነት ስጋት ሊነሳበት አይገባምም ነው ያሉት።
ግንባታውን የሚያከናውነው ኩባንያ ብር ተቀብሎ ሊፈርስ የሚችል ነገር ሊገነቡ አይችሉም ያሉት ምሁሩ፥ “የአካባቢው መሬት ይንቀጠቀጣል ተብሎ የሚወራውም ምንም እውቀት የሌላቸው የግብጻውያን ወሬ ነው” ብለዋል።
ዲዛይኑም ሆነ ግንባታው በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተና ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ በግድቡ ላይ የጥራት ጥያቄ ለማንሳት የሚያስችል አንዳችም አመክንዮ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግብጽ ጉዳዩን ፖለቲካዊ ከማድረግ ይልቅ ሳይንሳዊ ሁኔታው ላይ የተመሰረተ ድርድር ብታደርግ መልካም መሆኑንም ጠቁመዋል።
ግብፅ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ደረጃ ላይ የሚያስቀምጣት የከርሰ ምድር ውሃ ባለቤት እንደሆነችና ይህም ለምዕተ ዓመት የሚያገለግላት ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።