የሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት በየትኞቹ መስፈርቶች ሊመዘን ይችላል?
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት በተለያዩ መንገዶች ይታያል፡፡
የስነ-ምክክር መዛግብት እንደሚያሳዩት የተለያዩ ሀገራት ምክክርን ለማድረግ ሲወጥኑ በሒደቱ ፍፃሜ ላይ የሚጠብቋቸው ውጤቶች ይኖራሉ፡፡
በዚህ መሰረትም ሀገራዊ ምክክሩ የታሰበለትን ዓላማ ማሳካቱ ለውጤታማነቱ ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡
በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሀገራት የምክክር ሒደቱን የጀመሩበት ምክንያት እንደመለያየቱ መጠን የምክክር ውጤቶቻቸውም በዛው ልክ ሲለያይ ይስተዋላል፡፡
ከዚህም አኳያ የምክክር ሒደቶቹ ስኬታማነት እንደየዓውዱ የራሱን ቀለም ይዞ ይመጣል፡፡
ይህ ሲባል ግን የምክክር ሒደቶችን ስኬታማነት ወጥነት ባለው መንገድ መመዘን እንደማይቻል ተደርጎ መታሰብ የለበትም፡፡
በአንፃሩ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ የሚሰሩ ጥናቶች የምክክርን ስኬታማነት ለመመዘን የሚከተሉትን መነሻ መስፈርቶችን አስቀምጠዋል፡፡
1. የምክክሩ ውጤት በተለያዩ አካላት መካካል የነበሩ ስጋቶችን እና ቅራኔዎችን ለመፍታት ግልጽ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማምጣት ሲችል፤
2. በምክክር ሂደቱ ተሳታፊ የነበሩ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት በሒደቱ ለሚገኙ ውጤቶች ተገዢ ሲሆኑና የመፍትሔ ሀሳቦቹም ላይ ስምምነት ሲኖራቸው፤
3. በሀገራዊ ምክክሩ ውጤቶች ላይ የትኛውም አካል እጁን ሳያስገባና ግጭቶች ሳይፈጠሩ ብሎም ውጤቶቹ በታቀደው መሰረት ለትግበራ ሲቀርቡ፤
4. ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተጨባጭ የሆኑ የሰላም መንገዶችን ለመተግበር ስምምነቶች ላይ ሲደርሱ፤
5. የሀገራዊ ምክክር ውጤቶችን ወደ መሬት አውርዶ ለመተግበር የሚያስችል ግልፅ ፍኖተ ካርታ ተቀርፆ ለአፈፃፀም ሂደቱ የሚመጥን የክትትል እና ምዘና ስራዎች ሲሰሩ የሚሉት መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡