ጠ/ሚ ዐቢይ በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዋና ዋና የማሻሻያ ስራዎች ማካሄድ መቻሉን ገለፁ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ ምቹ፣ ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ እንዲቻል በማቀድ በተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ አማካኝነት ዋና ዋና የማሻሻያ ስራዎችን ማካሄድ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስ ቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ በተሰሩት የማሻሻያ ስራዎች ቁልፍ የሕግና የአስተዳደራዊ ለውጦችን ማስመዝገብ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
ከተደረጉት የሕግ ማሻሻያዎችም የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ማሻሻያ አዋጅ 1150-2011 እና ደንብ 461 -2012፣ በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚመሰረት የዋስትና መብት አዋጅ 1147/2011 እና ማስፈፀሚያ መመሪያ፣ የብድር መረጃ ቋት ማቋቋሚያ መመሪያ ቁጥር CRB-01-2012፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 11572011፣ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 1180-2012 እና የኢንቨስትመንት አዋጅ ለማስፈፀም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ኤሌክትሮኒክ ንግድና ግብይት አዋጅ፣ አዲስ የንግድ ሕግ (በሚኒስቴሮች ምክር ቤት የጸደቀ)፣ በውጭ ሃገራት በተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠት እና የመፈጸም ስምምነትን ለማጽደቅ የወጣ አዋጅ ቁጥር 1184-2012 እና የግልግል ዳኝነት እና የእርቅ አሰራርን ለመደንገግ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ እንደሚገኙበትም በፌስ ቡክ ገጻቸው አስፍረዋል