የኦሮሚያ ክልል የ2017 በጀት ከ285 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ ጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ ለ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈጸሚያ የቀረበለትን ከ285 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ጨፌው በሁለተኛ ቀን ውሎው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመከረ ሲሆን÷አዳዲስ ሹመቶችን እንዲሁም 6 ረቂቅ አዋጆችን አፅድቋል።
ጨፌው ተወያይቶ ያጸደቀው የመጀመሪያው አዋጅ የክልሉን የውሃ ሃብት አጠቃቀምና አስተዳደር የተመለከተ ሲሆን÷ይህም በክልሉ የውሃ ሃብት ላይ የተደቀኑ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንዲሁም ለምተው ለሁለንተናዊ ዜጎች ልማት ይውሉ ዘንድ ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
በመቀጠል የጸደቀው አዋጅ የክልሉን የደን አጠቃቀምና አስተዳደር የሚመለከት አዋጅ ሲሆን÷ይህም ተመናምኖ የቆየውን የደን ሃብት ለመጠበቅና ህገወጥ የደን ምንጠራን ለመቆጣጠር እንዲሁም የምግብና ስነምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል።
እንዲሁም በጉባኤው የኦሮሚያ ከተሞች ፕላንን ለመወሰን የተዘጋጀም አዋጅ የጸደቀ ሲሆን÷የከተሞችን በፍትሃዊነት የመልማትና የማደግ መብት ከማጎናፅፍ ባለፈ ምቹና ተወዳዳሪ ከተሞችን ለመፍጠር ያስችላል ነው የተባለው፡፡
በመራዖል ከድር