የሐረሪ ክልል የ2016 የሥራ አፈፃፀምና የ2017 ዕቅድ ግምገማ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የ2016 በጀት ዓመት የመንግሥት እና የፓርቲ ሥራዎች ዕቅድ አፈፃፀምና የ2017 ዕቅድ ዝግጅት ግምገማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ሮዛ ዑመር በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በ2016 በጀት ዓመት ለመፈፀም ከታቀዱት የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሰላም ሥራዎች አንፃር አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ለአብነትም÷ በቱሪዝም፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ገቢ አሰባሰብ፣ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ የኑሮ ውድነት ጫና ቅነሳ፣ ፅዳትና ውበት፣ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም የክልሉን ዘላቂ ሰላም አስጠብቆ በመጓዝ በኩል ስኬታማ ሥራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው÷ አባልና አመራሩ በፓርቲው እሳቤዎችና አቋሞች ላይ የጠራ ግንዛቤና አመለካከት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ፓርቲው “ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል በብሄራዊ ገዥ ትርክት እና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ ስልጠናዎች ስኬታማ እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት በጊዜ እና ጥራት በመገምገም ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጅት የሚደረግበት ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡