በጎፋ ዞን በተከሰተው ድንገተኛ የመሬት ናዳ የሟቾች ቁጥር 146 ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ትናንት በተከሰተው ድንገተኛ የመሬት ናዳ አደጋ የሟቾች ቁጥር 146 መድረሱ ተገለፀ፡፡
የዞኑ የመንግስት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ እና አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ መልሶ ማቋቋሚያ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሀብታሙ ፌተና አደጋውን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም÷ እስከ አሁን በተደረገው ፍለጋ ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ 96 ወንድ እና 50 ሴት በድምሩ የ146 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል ብለዋል፡፡
የነፍስ አድን ሥራው እና የአስክሬን ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው÷ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡