ከኢትዮጵያ ጋር ያለኝ የልማት ትብብር ይቀጥላል- አየርላንድ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አየርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የልማት ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ እንደምትሰራ የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሚሼል ማርቲን አረጋገጡ፡፡
በቅርቡ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የመጡት የአየርላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይና መከላከያ ሚኒስትር ሚሼል ማርቲን ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያና አየርላንድ ፍሬያማ ግንኙነት እንደነበራቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።
በእነዚህ ዓመታት አየርላንድና ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ውጤታማ የልማት ትብብር እንዳላቸው አውስተዋል፡፡
በተለይም በልማታዊ ሴፍቲኔት፣ በትምህርትና በጤና ዘርፍ አበረታች አጋርነት መፍጠር መቻላቸውን አንስተዋል፡፡
በቀጣይም በግብርና ዘርፍ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የምግብ ምርታማነትን ጨምሮ በሌሎች የልማት መስኮች ያሉ ትብብሮችን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የሀገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ቀጣይ የሁለቱ ሀገራት የቤት ሥራ መሆኑን አስገንዝበው÷ በዚህም ላይ አየርላንድ በትኩረት እየሰራች መሆኗን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያም እያካሄደች ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለሁለቱ ሀገራት ብሎም ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት መጠናከር ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።
አየርላንድ በቀጥታና በዓለም ባንክ በኩል እንዲሁም በአውሮፓ ኅብረት ማዕቀፍ ለሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ ገቢራዊ ለማድረግ እየተሠራ ያለውን የሽግግር ፍትሕ እንዲሁም ሀገራዊ ምክክር ከግብ ለማድረስ አየርላንድ ድጋፏን እንደምታጠናክር ገልጸዋል፡፡