የሰላም ካውንስል አባላት የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባሕር ዳር ከተማና ከሰሜን ጎጃም አስተዳደር ዞን የተመረጡ የሰላም ካውንስል አባላት የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሄዱ።
በመድረኩ የሰላም ካውንስሉ አባላት ከሁሉም የሰሜን ጎጃም ወረዳዎችና ከባሕር ዳር ከተማ የተሰባሰቡ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ሰብሳቢ አቶ ያየህይራድ በለጠ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ካውንስሉ ሕዝቡ የዘላቂ ሰላም ባለቤት ሆኖ ወደ ተሟላ ልማት ይመጣ ዘንድ በሁሉም ወገን ያሉ ሃይሎችን እንዲደራደሩና እንዲወያዩ የማመቻቸት ሚናውን ለመወጣት የሚበረታታ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ካውንስሉ ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁመው ለድርድርና ውይይት እንዲዘጋጁ የማመቻቸት ሚና ያለው ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችንና መንግሥትን ወደ ንግግር ለማምጣት የሰላም ካውንስሉ የማመቻቸት ሚናውን ለመወጣት ተስፋ የተጣለበት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።
የካውንስሉ ዓላማ ማመቻቸት ነው፤ አደራዳሪም ተደራዳሪም አይደለም ያሉት ሰብሳቢው÷ ሁለቱ ወገኖች የሚፈልጉትን አደራዳሪ መርጠው በሚፈልጉት ቦታ ተገናኝተው ውይይትና ንግግር እንዲያደርጉ የማመቻቸት ሥራ ይሠራል ሲሉ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ አሁን በተደረሰበት የታሪክ ምዕራፍ የትውልዱን አደራ ለመወጣት የሰላም ካውንስሉ ዓላማ ለማስፈጸም ተሳታፊ እንዲሆንም ጠይቀዋል።
መንግሥትም ሆነ በጫካ የሚገኙ ወገኖች ወደ ድርድርና ውይይት በመምጣት ታሪክ እንዲሠሩ ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የሰላም ካውንስሉ ከአባላቱ ጋር የእቅድ ትውውቅ ያደረገ ሲሆን÷ ዓላማው ጦርነትን በማስቆም ሰላም ማስፈን በመሆኑ ከክልል እስከ ቀበሌ በተዘረጋ መዋቅር ሃሳቦችን በማዋጣት የጋራ መፍትሔ ለማፈላለግ ጠንክሮ እየሠራ ነው ተብሏል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ