Fana: At a Speed of Life!

ከ18 ሺህ በላይ የሽጉጥ ጥይቶችን ወደ አዲስ አበባ ሊያስገቡ ሲሉ የተያዙ በጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መነሻውን አማራ ክልል በማድረግ ከ18 ሺህ በላይ የቱርክ ሽጉጥ ጥይቶችን በተሽከርካሪ በመደበቅ ወደ አዲስ አበባ ሊያስገቡ ሲሉ በብሔራዊ መረጃ ደህንትና በፀጥታ አካላት ክትትል ተይዘዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሰሜን ሸዋ ዞን ዐቃቤ ህግ ሲሳይ ያቆብ እና ትዕግስት እባቡ በተባሉ ግለሰቦች ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 አንቀጽ 22 ንዕስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 49 ንዑስ ቁጥር 2 ስር፤ በተጨማሪም በአዋጅ ቁጥር 234/2013 ስር እንዲሁም የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 2 እና 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ መነሻውን አማራ ክልል በማድረግ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳቶች እና 33 ኩንታል በቆሎ በጫነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ውስጥ 18 ሺህ 968 የቱርክ ሽጉጥ ጥይቶችን ደብቀው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሊገቡ ሲሉ በብሔራዊ መረጃ ደህንነት እና በዞኑ እና በሌሎች የፀጥታ አካላት ክትትል በሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ ቆርባ ኢሼ ቀበሌ ኬላ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸው በክስ ዝርዝሩ ተገልጿል።

በዚህ መልኩ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት በዐቃቤ ህግ የቀረበው የክስ ዝርዝሩ ለተከሳሽ እንዲደርስ በማድረግ በችሎት በንባብ ካሰማ በኋላ ተከሳሾቹ የክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል መነሻ በዐቃቤ ህግ የቀረቡ ማስረጃዎችን ተመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል አለመቻላቸው ተገልጾ አንደኛ ተከሳሽ በቀረበበት በ1ኛ እና በ3ኛው ክስ ጥፋተኛ በማለት በሁለተኛው ክስ ግን ነጻ ተብሏል።

ሁለተኛ ተከሳሽ በቀረበባት ክስ ጥፋተኛ ተብላለች።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየቶችን በመያዝ አንደኛ ተከሳሽን በ10 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽን ደግሞ በ4 ዓመት ጽኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ወስኗል።

የተያዙ ንብረቶችም እንዲወረሱ ታዟል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.