Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአሳቢ ወጣት ዜጎቿ ተስፋ አላት- ጠ/ ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ወደፊት በሚያልሙ አሳቢ ወጣት ዜጎቿ ተስፋ አላት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ ”አምስት ሚሊየን ኮደርስ” መርሐ-ግብርን በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል፡፡

የመርሐ-ግብሩን መጀመር አስመልክቶም በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ ኢትዮጵያ ወደፊት በሚያልሙ አሳቢ ወጣት ዜጎቿ ተስፋ አላት ብለዋል፡፡

ዛሬ በይፋ የጀመርነው የ ”አምስት ሚሊዮን ኮደርስ” መርሐ-ግብርም ታላቅ ዕድል ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ወጣቶች በመርሐ-ግብሩ በመመዝገብ ክኅሎት እንዲያገኙና ዓለም አቀፍ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) እንዲያገኙ ሁሉም እንዲያበረታታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለታላቁ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት ትብብር ላደረጉት ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግሥት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አምስት ሚሊየኖቹ ኮደሮች ሀገር በቀል መፍትሔዎችን የሚሰጡ ብቻ ሳይሆኑ÷ ለአኅጉራችን የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቁም ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የ ”አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች” መርሐ-ግብር በኢትዮጵያ እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መንግሥታት መጀመሩን እና የዲጂታል ሥራ ክኅሎትን የማሳደጊያ የትብብር ፕሮጀክት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

በማደግ ላይ ባለው ዲጂታል ኢኮኖሚ ከባቢ የመጪው ትውልድ ኢትዮጵያዊያንን ለማብቃት ታልሞ መጀመሩም ተጠቅሷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሳይንስ ሙዚየም መርሐ-ግብሩን የዲጂታል እውቀት ክፍተትን ለማጥበብ የሚያስችል የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 አካል አድርገው በይፋ ማስጀመራቸውም ተገልጿል፡፡

መርሐ-ግብሩ በፈረንጆቹ 2026 አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክኅሎት ያስጨብጣል ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.