Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ለሰላም አማራጭ የተከፈተው በር አሁንም የማይዘጋ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰላም አማራጭ የተከፈተው በር አሁንም የማይዘጋ መሆኑን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገልጿል፡፡

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው÷ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በመሠራታቸው ክልሉ አሁን ለሚገኝበት አንጻራዊ ሰላም መድረሱን ገልጸዋል።

የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚነትና የተሟላ የልማት ተሳታፊነቱን የሚገድቡ ሁኔታዎች አሁንም ሙሉ በሙሉ አለመቀረፋቸውን ተናግረዋል።

ችግሩ በሕግ ማስከበር ሥራ ብቻ የማይፈታ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት የሰላም አማራጭን በመዘርጋት የሰውን ሞት ለማስቀረትና ወደ ዘላቂ ሰላም ለመድረስ ሕዝቡን እስከ ታች ወርዶ ማወያየት መቻሉን አንስተዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ወጣቶችና ሴቶች የተሳተፉባቸው ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንሶችም የሕዝቡን ፍላጎት ለይቶ በማወቅ በገለልተኝነት የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ያስቻለ የተሻለ የሰላም አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን የልማት ሥራው እንዳይደናቀፍ ከ6 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል፣ ተማሪዎችን በማስፈተን፣ ተቋማት እንዲሠሩ በማድረግ ውጤታማ የሰላምና የፀጥታ ሥራ ተከናውኗልም ብለዋል፡፡

ጫካ የገቡ ወገኖች የአማራ ሕዝብ ሰላም የሚረጋገጠውም ሆነ ጥያቄዎቹ የሚፈቱት በሰላማዊ አማራጭ በመሆኑ ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው እንዲወያዩ ለማድረግ ሕዝቡ የራሱን የሰላም ካውንስል አደራጅቶ ውይይትና ድርድርን ለማመቻቸት መሥራቱን መንግሥት እንደ ጥሩ አማራጭ የተመለከተው መሆኑንም ሃላፊው ተናግረዋል።

የሰላም አማራጭን ገፍተው ስለ ሰላም የሚሰብኩ ወገኖችን የሚያሰቃዩና የሚያንገላቱ የታጠቁ ቡድኖች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ቡድኖቹ ሰሞኑን በሰሜን ጎጃም ዞን ደቡብ ሜጫ ወረዳ ገርጨጭ ከተማ ላይ በተለያዩ ሥራዎች ከባሕር ዳር ከተማ ቆይተው የተመለሱ የከተማዋን 15 ነዋሪዎች ከየቤታቸው በማውጣት የሰላም ካውንስል አባላት ናችሁ በማለት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዳንገላቷቸው ገልጸዋል።

በዚህ ሳያበቁ የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መርጌታ ግሩም፣ የሀገር ሽማግሌ አቶ አዘነ አድማሱ፣ የሀገር ሽማግሌ አቶ አስማማው አቤ እና ወ/ሮ የኔአየሁ ዳኛው የተባሉ እናትን መግደላቸውን አስታውሰዋል፡፡

በጥፋት ቡድኑ የግፍ ሰላባ ለሆኑ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን የተመኙት ሃላፊው÷ አሁንም ቢሆን ለሰላም አማራጭ የተከፈተው በር የማይዘጋ መሆኑንና የሕዝብን የተሟላ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.