በክልሉ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል – አቶ ሙስጠፌ መሐመድ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ገለፁ።
በክልሉ ምክር ቤት 6ኛ የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የክልሉ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በርዕሰ አስተዳድሩ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በገቢ አሰባሰብ፣ በአርብቶ አደር ልማት፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች የልማት ዘርፎች የተሻሉ አፈፃፀሞች ተመዝግበዋል።
በሌማት ትሩፋት፣ መስኖን በማጎልበት እና የገበያ ተኮር ሰብሎች ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።
የገቢ አቅምን ለማሳደግ በተከናወኑ ስራዎች በዓመቱ ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ13 ቢሊዮን 500 ሚለዮን ብር በላይ መሰብሰቡንና የእቅዱ 84 ነጥብ 5 በመቶ መመፈጸም መቻሉን ገልጸዋል።
በዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ3 ነጥብ 7 ቢልዮን ብር ብልጫ እንዳለውም መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
118 የተለያዩ የልማት ፕሮጅክቶች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።
የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን በሪፖርታቸው ገልጸዋል።
የትምህርት ጥራት ከማጎልበትና የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አንጻርም አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።