Fana: At a Speed of Life!

ሴቶች በሀገራዊ ምክክሩ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ በትኩረት እንደሚሰራ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሴቶች በሀገረ-መንግስት ግንባታም ሆነ በሀገራዊ ምክክሩ የተሟላና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው በትኩረት እንደሚሰራ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ጥምረት ለሴቶች ድምጽ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በሺዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት አጀንዳዎቻቸውን ሲያሰባስብ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

የሴቶችን አጀንዳም ጥምረቱ ለብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በዛሬው ዕለት አስረክቧል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በሀገራዊ ምክክር መሰረታዊ ችግሮችን በውይይት የመፍታት እሳቤ አሁን ላይ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

ሚኒስቴሩ በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች የተሟላና ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ግንባር ቀደም ተጎጂዎች ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመው÷ አካታች ምክክር ማካሔድ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳዎች የአሁንና የወደፊት ሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በበኩላቸው ÷ አሸናፊ ሆነን እንውጣ ከተባለ መመካከር አለብን፤ በምክክሩም ሴቶችን ይዘን መውጣት አለብን ብለዋል።

የሴቶች አጀንዳ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አጀንዳ እንደሆነ አጽንኦት መስጠታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.