የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ለመዘግየቱ የፕሮጀክት አስተዳደር ችግሮች ዋነኛ እንቅፋት እንደነበረ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ለመዘግየቱ የፕሮጀክት አስተዳደር ችግሮች ዋነኛ እንቅፋት እንደነበረ የቀድሞው የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ተናገሩ፡፡
አቶ ሞቱማ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ከለውጡ በፊት በፕሮጀክቱ ላይ የቦርዱ ሪፖርት ከግንባታ ሂደቱ ጋር ጭምር ያልተናበበ የውሸት አፈጻጸም ይገልጽ ነበር ብለዋል ።
የአመራር ክፍተቱም የፕሮጀክት ፍጥነቱን የያዘ እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ሞቱማ ፤ከግብጽ ጋር በሚደረግ ድርድር ግን የቦርዱ ጣልቃ ገብነት እንዳልነበረ ተናግረዋል ።
በጊዜው ከ40 እስከ 45 በመቶ የፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን ፤ የግድቡን ግንባታ የሚከታተለው ቦርድ ለመካኒካል ስራዎች ሜቴክን ከስራው ጋር አጋፍጦ የተስተዋሉ ችግሮችን ለማንሳት ሚኒስቴሩ ቢሞክርም ሰሚ አጥቶ እንደነበር አስታውሰዋል ።
በተሟላ አቅም እና ልምድ የመስራት ሁኔታ ባለመፈጠሩም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውሳኔ ሰጪ መሆኑ ቀርቶ ዳር መቆሙንና ቦርዱ ሂደቱን መቆጣጠሩንም ያስታውሳሉ ።
ይህ ስልጣን እና ተግባርን ጠቅልሎ የመውሰድ ሂደት ደግሞ በፕሮጀክቱ ለተስተዋለው መዘግየት ምክንያት ሆኖ በመሬት ላለው የግንባታ ሂደት እና የሪፖርት አቀራረብ መራራቅ ዳርጓልም ነው ያሉት ።
የደን ምንጣሮ ይደረጋል ተብሎ በወቅቱ በቦርዱ የተሰጠው መግለጫም የህዝብን ፕሮጀክት በሀሰተኛ መረጃ የማዘናጋት ሂደት እንደነበረም ገልጸዋል ።
አሁን ላይ የካይሮ ሰዎች በድርድሩም ሆነ በፕሮፓጋንዳ የሚደርጉት የማጥላላት እንቅስቃሴ የግድቡ ግንባታ ሂደት የፈጠረው መሆኑን አስረድተዋል ።
አቶ ሞቱማ አያይዘውም ከውጭም ሆነ ከውስጥ በግድቡ ግንባታ ላይ የሚነሱ አሉባልታዎችን በአንድነት በመቆም መመከት እንደሚገባ አንስተዋል።
በሀይለየሱስ መኮንን