በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ2 ሚሊየን ዜጎች ነፃ የጤና አገልግሎት ይሰጣል- ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላ ሀገሪቱ ለሁለት ወራት በሚሰጠው የክረምት ሕክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለ2 ሚሊየን ዜጎች ነፃ የጤና አገልግሎት እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በበጎ ፈቃድ የሚከናወነው ሀገር አቀፍ ነፃ የክረምት የጤና ምርመራ፣ የምክርና የሕክምና አገልግሎት መርሐ-ግብር በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ እና በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ዛሬ መጀመሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ ነፃ ሕክምና በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁለት ወራት ይካሄዳል፤ በዚህም ለ2 ሚሊየን ዜጎች ነፃ የጤና አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ከነፃ ሕክምና በተጨማሪ የደም ልገሳ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች የቤት እድሳትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም የችግኝ ተከላ እንደሚካሄድ አብራርተዋል፡፡