የሞጆ ደረቅ ወደብን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ማዕከል በማድረግ የሎጂስቲክስ ስራዎችን ለማሳለጥ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሞጆ ደረቅ ወደብን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ማዕከል በማድረግ የሎጂስቲክስ ስራዎችን ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን አስታውቋል።
የማሪታይም ባለስልጣን አመራሮችና ሠራተኞች፣ የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሰራተኞች እና በፕሮጀክቱ የሚሰሩ የውጭ ዜጎች በሞጆ ደረቅ ወደብ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፋ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።
ዛሬ በሞጆ ደረቅ ወደብ የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደረቅ ወደቡን ከአረንጓዴ ልማት ጋር ለማስተሳሰር የሚደረገው ስራ አካል ነው ብለዋል።
የሞጆ ደረቅ ወደብን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ማዕከል በማድረግ የሎጂስቲክስ ስራዎችን ለማሳለጥ ዘርፈ ብዙ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም በወደቡ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ስራን በማጠናከር የሎጂስቲክስ ስራዎችን በአስተማማኝ መልኩ ማከናወን ያስችላል ነው ያሉት።
የሞጆ ደረቅ ወደብ ሃላፊ ተወካይ አቶ ብርሃን ኪዳን በበኩላቸው፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ሚዛንን በማስጠበቅ አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።
የባለስልጣኑና የደረቅ ወደቡ ሰራተኞች ዛሬ ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን መትከላቸውን ገልጸው፥ በቀጣይም የደረቅ መደቡን የማልማት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የተተከሉ ችግኞችን ለመንከባከብም ኮሚቴ ተዋቅሮ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በችግኝ ተከላው የተሳተፉት ሌሎች አመራሮች እና ሰራተኞኝ አረንጓዴ አሻራቸውን በማሳረፋቸው መደሰታቸውን እንደገለጹ የባለስልጣኑ መረጃ አመልክቷል።