የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ የአዘጋጆች ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ላለፉት አራት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ የአዘጋጆች ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡
ስብሰባው በ2025 በስፔን በሚካሄደው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ላይ አጀንዳዎችን እና በጉባኤው የሚቀርቡ ዘላቂ ልማት ግብ መፍትሄዎችን ለመለየት ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በጉባኤው የውስጥ ሀብት ማሰባሰብን በተመለከተ፣ የእዳ አያያዝን፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት እና የልማት ትብብርን በተመለከተ ምክክር ተደርጓል፡፡
በጉባኤው ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች በዘላቂ የልማት ፋይናንስ አተገባበር ላይ የሚያደርሱትን አሉታዊ ተፅእኖ በመገንዘብ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የጋራ ጥረቶች እንደሚያስፈልጉ አፅንኦት ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል የሀብት ብዝሃነትን ማጎልበት እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ ፋይናንስን ለማሳደግ አዳዲስ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ እና ይህም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ በጉባኤው ተገልጿል፡፡
የብድር ጫና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የገቢ ሁኔታ ላይ ጫና ስለሚያሳድር የእዳ ጫናን ለማስተካከል የብድር መልሶ ማዋቀር እና ዘላቂነት ላለው የእዳ አያያዝ ጥብቅ የብድር ፖሊሲ እርምጃዎችን መተግብር እደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የውስጥ የገቢ አቅምን ለማሳደግ የታክስ ስርዓቱን ዲጂታል ማድረግ እና የታክስ መሰረትን ማስፋት እንዲሁም የግሉን ዘርፍ እምቅ አቅም መጠቀም እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡
በመጨረሻም ዘላቂ የልማት ግቦችን እና አጀንዳ 2030ን ለማሳከት ባለብዙ ወገን ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ መገለፁን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡