የክልሉ መንግሥት የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም እየሠራሁ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን በመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለመቋቋም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
አቶ ጥላሁን በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦችን እና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አፅናንተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም የክልሉ መንግሥት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ እና በአደጋው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ሥራም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ተጎጅዎችን ለመደገፍ ርብርብ ላደረጉ ክልሎች፣ ከተማ አሥተዳደሮች እና ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከፌዴራል መንግሥት፣ ከአጎራባች ዞኖች እና ክልሎች እንዲሁም ከሌሎች ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች ምግብ፣ አልባሳት፣ መድኃኒት እና ሌሎች ድጋፎች እየቀረቡ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
በታሪኩ ለገሰ፣ ማቱሣላ ማቴዎስ እና መለስ ታደለ