የምክክር ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍን አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ክልል አቀፍ የምክክር ምዕራፍ አስጀምሯል።
በተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 300 በላይ የህብረተሰብ ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ይገባል የተባሉ ወሳኝ አጀንዳዎችን ለማሰባሰብ ይረዳል ተብሏል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም÷ ኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካዊ ውጣውረድና ልዩ ልዩ ሂደቶች አልፋ እዚህ ደርሳለች፤ የሚታዩትን የሀሳብ ልዩነቶች በግጭት ለመፍታት የሞከርንባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው ብለዋል።
በሂደቱም ጊዜያዊ አሸናፊና ተሸናፊ በመፍጠር መልሰው እያቆጠቆጡ እንደሀገር በግጭት ኖረናልም ሲሉ ተናግረዋል።
የጋምቤላ ህዝብም በዚህ ሂደት ያለፈ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የሀይል አማራጭ እንደማያዋጣ የትናንት እና የዛሬ ታሪኮች ምስክር ናቸው ብለዋል።
ችግሮችን ከምንጫቸው ለማድረቅ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን አጀንዳ በመቅረፅ አዲስ ታሪክ የሚጻፍበት ወቅት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
በዓለምሰገድ አሳዬ