የአዲስ አባባ ከተማ ለጎፋ ዞን ተጎጂዎች በ2ኛ ዙር ከ51 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በ2ኛ ዙር ከ51 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ ከጎናችን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷የውጪ መንግስታት፣ ክልሎች፣በርካታ ድርጅቶች፣ታዋቂ ግለሰቦችና መላው ኢትዮጵያዊ ከጎናችን ነው ብለዋል፡፡
ለድጋፉ ምስጋና አቅርበው የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደርን ድጋፍ ቦታው በመገኘት ያስረከቡት የአስተዳደሩ ተወካይ አቶ በላይ ደጀን በአደጋው የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡
ከተማ አስተዳድሩ ከሁሉም ክፍለ ከተማ የተዋጣ በጥሬ ገንዘብ 6 ሚሊየን እንዲሁም 45 ሚሊየን ብር በአይነት በድምሩ ከ51 ሚሊየን ብር በላይ በሁለተኛ ዙር ድጋፍ ማድረጉን ተወካዩ ገልፀዋል፡፡