Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እና ቻይናን ትብብር በይበልጥ ለማጎልበት እንሠራለን – ቻይናውያን ጋዜጠኞች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና ቻይና ትብብርና ወዳጅነት እንዲዳብርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱም በይበልጥ እንዲጎለብት በሙያችን እንሠራለን ሲሉ ቻይናውያን ጋዜጠኞች ገለጹ፡፡

ከቻይና ‘ፒፕልስ ደይሊ’ ጋዜጣ የተውጣጣ የጋዜጠኞች ልዑክ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማስፋፊያ ተርሚናልን ጨምሮ በቻይና በቀል ተቋራጮች የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን ጎብኝቷል።

የኢትዮጵያና ቻይና ወዳጅነት በየዘመናቱ እየተጠናከረ መምጣቱን የገለጸው ልዑኩ÷ ሀገራቱ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ትስስር መገንባታቸውን አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ እየታየ ያለው ፈጣን ለውጥም ይህንን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያዩት ነገር ከነበራቸው ዕሳቤና ከጠበቁት አንጻር ፍጹም የተለየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጎዳናዎች መልክ ስለ ኢትዮጵያ የነበራቸውን አመለካከት እንዲለውጡ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተመለከቱት ዕድገት እንዳስደመማቸው በመግለጽ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ ዕድገትና ለኢትዮጵያውያን ኑሮ መሻሻል በሚበጁ ፕሮጀክቶች ላይ ዐሻራቸውን እያሳረፉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የሀገራቱን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እየጎለበተ መምጣት ማሳያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ትብብርና ወዳጅነት እንዲዳብርና፤ የሕዝብ ለሕዝብ ግነኙነቱም ይበልጥ እንዲጎለብት በሙያቸው እንደሚሠሩም ነው ያረጋገጡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.