የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ሽልመት የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዓለም የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ሽልመት የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተካሂዷል።
በደስታ መግለጫ መርሃ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የፌዴራልን የክልል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በፕሮግራሙ ባደረጉት ንግግር የዓለም የኖቤል የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሽልማታቸውን ተቀብለው ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ሲገቡ ህዝቡ የሚገባቸውን የጀግና አቀባበል ያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተቀዳጁት የሰላም የኖቤል ሽልማትም ሀገራችን በዓለም መድረክ ከፍ እንድትልና ዜጎቿም ኩራት እንዲሰማን አድርጓል ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ።
ከዚህ ባለፈም ሽልማቱ ለቀጠናው ሀገራት ብሎም ለመላው ሰላም ፈላጊ ማህበረሰብ ከፍተኛ ተነሳሽነትን እና ጥንካሬን ያጎናጸፈ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ያነሱት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ በለውጡ ላይ የሚጋረጡ ችግሮችን በአንድናትና በመተባበር ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሃሳብ መለያየት ጠላትነት አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት መፍታት አስፋላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በበኩላቸው የኖቤል ሽልማታቸውን ተቀብለው ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ላደረገላቸው ሁሉ ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል።
ለሽልማቱ እውን መሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱት ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ለሀገሪቱ ህዝቦችም ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠልም ዜጎች በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ እንዲሁም በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጠሮ ሃብት የበለጸገች ሀገር መሆኗን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ያለውን እምቅ እና ያልተነካ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የብልፅግና ጎዳናውን ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
ከልመና ወጥተን ወደ ብልፅግና ለመሸጋገርም ከመላው የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ህዝቦች ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም ዜጎች ምክንያታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ እርስ በርስ መናቆረን በማስወገድ ለሀገሪቱ እድገትና ብልጽግና ጠንክረው በመስራት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በመላኩ ገድፍ