Fana: At a Speed of Life!

በአንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ይኖራል – ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፣ ሐምለሌ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የወንዞች ሙላት፣ ቅጽበታዊ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት የሚያስከትል ከባድ ዝናብ ስለሚኖር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

ኢንስቲትዩቱ በቀጣዮቹ 10 ቀናት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በሁሉም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ በተስፋፋና በተጠናከር ሁኔታ ቀጣይነት እንደሚኖራቸው አስታውቋል፡፡

በተለይም በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምስራቅና እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ጠንካራ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖራቸው አሀዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል፡፡

በተጨማሪም አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች ላይ በመነሳት በምዕራብ፣ በሰሜንና በመካከለኛው የሀገሪቱ ስፍራዎች ላይ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ነው የተባለው፡፡

በመሆኑም ለወንዞች ሙላትና ለቅጽበታዊ ጎርፍ መከሰት እንዲሁም የመሬት መንሸራተት የሚያስከትል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ስለሚኖር ከወዲሁ ማሕበረሰቡና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄና ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡

በሚቀጥሉት 11 ቀናት ከትግራይ ክልል ምስራቅ፣ ማዕከላዊ፣ ሰሜን ምዕራብ፤ ምዕራብ እና ደቡብ ምስራቅ ዞኖች፤ ከአማራ ክልል ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ሰሜን፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም፣ ዋግኽምራ፣ አዊ፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን፤ ከአፋር ክልል ቅልበቲ፣ ፈንቲ፣ ሃሪ እና ጋቢ ዞኖች፤ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል፣ አሶሳ፣ ማኦ ኮሞ እና ካማሺ ዞኖች፣ ከጋምቤላ ክልል ኑዌር፣ አኝዋክ፣ ማጃንግ እና የኢታንግ ልዩ ዞን ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ መባሉን የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ፣ ኢሉ አባቦር፣ ጅማ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ሐረርጌ፤ አዲስ አበባ፤ ድሬዳዋና ሐረሪ፤ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ፣ ምስራቅ ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ሀላባ፣ ከምባታ፣ ስልጤ፣ የም ዞኖች፣ ጠምባሮ፣ ቀቤና እና ማረቆ ልዩ ወረዳ፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮ፣ ኮንታ ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ እና ባስኬቶ ዞኖች፤ በሲዳማ ክልል ዞኖች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ከዕለት ወደ ዕለት ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ከኦሮሚያ ክልል የባሌ እና ምስራቅ ባሌ ሰሜናዊው ክፍል፣ ምስራቅ ሐረርጌ፣ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች፤ ከሶማሌ ክልል ሲቲ፣ ፋፋን፣ ጀራር፣ ኤረር እና ኖጎብ ዞኖች፤ ከአፋር ክልል አውሲ እና ማሂ ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ፣ አሪ፣ ደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.