Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ እየመከረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ እያካሄደ ባለው አስቸኳይ ስብሰባ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለመጀመሪያው ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ እድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለማጽደቅ እየመከረ ነው፡፡

ምክር ቤቱ 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።

ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር በብድር የተገኘው የ500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን የሪፎርም ስራዎች ለመደገፍና የፌደራል መንግስትን የ2017 በጀት በቀጥታ ለመደገፍ የሚውል ነው።

ብድሩም ከወለድ ነፃ እና በረጅም ዓመታት የሚከፈል በመሆኑ ከኢትዮጵያ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣምና ጫናውም ያልበዛ መሆኑን የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ ባቀረቡት አጭር መግለጫ ተናግረዋል።

ብድሩ የስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ ይጠናቀቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊስ ትግበራ መግባቷን ተከትሎ ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር 1 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍና ብድር ማፅደቁ ይታወቃል።

ምክር ቤቱ የብድር ስምምነቱን ለማጽደቅ የወጣውን አዋጅ መርምሮ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.