ባለፉት አራት ወራት ከወጪ ንግድ 916 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 3፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2012 በጀት ዓመቱ አራት ወራት ከግብርና፣ ከማምረቻ እና ከማዕድን ምርቶች ዘርፍ 916 ነጥብ 21 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተገኘ፡፡
በበጀት ዓመቱ አራት ወራት 1 ነጥብ 07 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነው 916 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱ የተገለፀው፡፡
አፈፃፀሙ ከ2011 ዓ.ም ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 814 ነጥብ 73 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ 101 ነጥብ 48 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብልጫ እንዳለው የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ከተያዘላቸው ዕቅድ በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡት የወጪ ምርቶች አበባ፣ የብዕርና አገዳ እህሎች፣ የተፈጥሮ ሙጫና እጣን፣ ጫት፣ እና የኤሌክትሪክ ምርቶች ናቸው፡፡
የዕቅዳቸውን ከ75 በመቶ እስከ 99 በመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች ደግሞ ባህር ዛፍ፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ሰም፣ ቡና፣ ታንታለም እና የቅባት እህሎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
እንዲሁም ከዕቅዳቸው ከ50 ከመቶ እስከ 74 ከመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች አትክልትና ፍራፍሬ ፣ ስጋ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የቁም እንሰሳት፣ ወተትና የወተት ተዋፅኦ እና ሻይ ቅጠል ናቸው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ከተያዘው ዕቅድ አንጻር በውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ገቢ ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲስቲካልስ፣ ማር፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ ቅመማ ቅመም፣ ሌሎች ማዕድናት፣ ዓሳ፣ ሥጋ ተረፈ ምርት፣ ወርቅ እና ብረታ ብረት መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡