የሐይማኖት ተቋማት ሰላምን ለማረጋገጥ አስተዋጽአቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው – ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐይማኖት ተቋማት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔና የዕውቅና መድረክ “በጎ ለዋሉልን እናመስግን፤ ሰላማችንን እንጠብቅ” በሚል መሪ ሀሳብ እያካሄደ ነው።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በወቅቱ እንደገለጹት÷ የሐይማኖት መሪዎች በምዕመናን ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው ለዘላቂ ሰላም መስፈን መሥራት አለባቸው።
የሐይማኖት ተቋማት በሀገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ እያከናወኑ ያለውን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የሐይማኖት ተቋማት ሀገርን በዘመናት ለማስቀጠል ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ተቋማቸው በሰላምና አብሮነት ዙሪያ ከኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር እያከናወነ ያለውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጉባዔው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ÷ ጉባዔው በሰላምና መከባበር እሴት ግንባታ ላይ በትብብር ለመሥራት የተመሠረተ መንፈሳዊ ተቋም ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለሰላም፣ መከባበርና አብሮነት እሴቶችን ማጎልበት የጀመረውን ጥረት ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥም አረጋግጠዋል።