ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አማራ ክልልን ከነበረበት ሁኔታ የሚያሻግርና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ ለመተግበር ዕቅድን በኃላፊነት መፈጸም እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስገነዘቡ፡፡
የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩም ክልሉን በተለያየ መስክ ለማሳደግና ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም የሚተገበር ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ላለው አመራር መቅረቡ ተገልጿል፡፡
መነሻን አውቆ መድረሻን ተረድቶ ለመሥራት ዕቅድ መሰረታዊ መሆኑን የገለጹት በመድረኩ የተገኙት አቶ ተመስገን÷ ለተፈጻሚነቱም የሁሉም ትኩረትና ፈጻሚነት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዕቅዱ የክልሉን ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ የላቀ ውጤት ለማምጣት ታስቦ መዘጋጀቱን አመላክተው÷ ለተግባራዊነቱ የክልሉን ሐብት በትክክል የተረዳ በዕውቀት የተደገፈ ሥራ ከአመራሩ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ክልሉን ከነበረበት ሁኔታ የሚያሻግር፣ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ እውን ለማድረግ የተዘጋጀውን ዕቅድ በኃላፊነትና በመናበብ መተግበር እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
በፍሬሕይወት ሰፊው