Fana: At a Speed of Life!

ለሽብር ወንጀል መዘጋጀት ክስ የቀረበባቸው 14 ግለሰቦች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በእነ መላክ ምሳሌ መዝገብ የሽብር ወንጀል ዝግጅት የተከሰሱ ከ20 ግለሰቦች መካከል 14 ተከሳሾች በቀረበባቸው የክስ ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡

ቀሪ 6 ተከሳሾች ደግሞ በቀረበባቸው ክስ ላይ ወንጀል ስለመፈጸማቸው በዐቃቤ ህግ በቂ ማስረጃ አልቀረበም ተብሎ በነጻ ተሰናብተዋል።

ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የህገ መንግስትና በህገ መንግስት ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮች የሚመለከተው ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች የፌደራል ዐቃቤ ህግ በእነ መላክ ምሳሌ መዝገብ 20 ተከሳሾች ላይ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማሳካት በአካል በመገናኘት በመደራጀትና በመወያየት እንዲሁም መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም በዋትስአፕ የበይነመረብ መገናኛ ዘዴ ላይ ዕቁብ የሚል ስም የተሰጠው መወያያ በመክፈት በቡድን በመወያየት፣ የአማራ ብልፅግና፣ ህወሐትና የኦሮሞ ብልፅግና ጠላቶቻችን ስለሆኑ በሃይል እርምጃ መጥፋት አለባቸው የሚል ስምምነት በማድረግ፣ አምስቱ የአማራ አናብስቶች ንቅናቄ የተባለ ህቡዕ ድርጅት በመመስረት፣ ለድርጅቱ ፋይናንስ ማፈላለግ እንዲሁም የሃይል ጥቃት የሚጀመርበት ስፍራዎችን በመምረጥ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ዝግጅት ማድረግ በሚል ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም የሽብር ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

በክሱ ጭብጥ ላይ በአ/አ ከተማ ህዝባዊ አመፅ ለማስነሳት በመዘጋጀት፣ በህዝባዊ አመፁ ወደ ቤተ መንግስት አቅጣጫ በሚታለፍበት አካባቢ ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ነዳጅ ማደያዎች እና የመንግስት ተቋማትን በማቃጠል ጉዳት እንዲደርስ እንዲደረግ እና በዚህም መንግስት መከላከል እንዳይችል አቅጣጫ በማስቀመጥ መስማማት እና በጥቅሉ ለሽብር ተግባር መዘጋጀት የሚሉ ዝርዝሮች ተካትተዋል።

ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ ከቀኑ 8:00 መገናኛ አካባቢ መተባበር ህንጻ 4ኛ ፎቅ ላይ የህቡዕ አደረጃጀት አባላትና አመራሮች ህዝባዊ አመፅ ማስነሳትን መሰረት ያደረገ ስብሰባ በማካሄድ፣ የውሃ ልክ፣ አሸዋ፣ ሲሚንቶ፣ ግንበኛ፣ የሚል መጠሪያ ኮድ በመሰጣጣት፣ ገንዘብ ማሰባሰብ፣ የጦር መሳሪያ እና ለወታደራዊ ምግብ ግዢ ለማዋል መዘጋጀት፣ ህዝቡን ለማሸበርና መንግስትን ለማስገደድ በማሰብ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ዝግጅት ማድረግ የሚሉ ነጥቦችን በአንደኛው ክስ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ተካቶ የቀረበ ሲሆን÷ በ5ኛ እና በ14ኛ ተከሳሾች ላይ ደግሞ በሁለተኛው ክስ ፍቃድ የሌለው የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት የሚል በክሱ ላይ ጠቅሶ በዝርዝር ቀርቦ ነበር።

ይህ የክስ ዝርዝር በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች ዋስትና እንዲፈቀድላቸው በጠበቆቻቸው አማካኝነት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም በማለት ክርክር ተደርጓል።

የግራ ቀኝ ክርክሮችን የመረመረው ፍርድ ቤቱ 19 ተከሳሾች ላይ ከቀረበባቸው የሽብር ክስ ውስብስብነት አንጻር ቢወጡ የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው ሊቀርቡ አይችሉም የሚለውን ግምት በመያዝ የዋስትና ጥያቄያቸው በሙሉ ድምጽ ውድቅ አርጓል።

በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ በዚሁ መዝገብ ቅድስት የተባለች 17ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ግን እራሳቸውን ለመንከባከብ አቅም የሌላቸው የአራት ልጆች እናት በመሆኗ እና የህጻናቶች የቤተሰብን እንክብካቤ የማግኘት ህገ-መንግስታዊ የመብት ድንጋጌዎችን ታሳቢ በማድረግ እና ተከሳሿ የዋስትና ግዴታዋን አክብራ ልትቀርብ ትችላለች የሚል ግምት ተይዞ በ50 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንድትፈታ በሙሉ ድምፅ ብይን ሰጥቷል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል መሰረት የዐቃቤ ህግ ምስክር ቃልና የሰነድ ማስረጃን ተመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት 2ኛ፣ 7ኛ፣ 11ኛ፣ 15ኛ፣ 18ኛ እና 19ኛ ተከሳሾች ላይ በቀረበው ክስ የተጠቀሰ የወንጀል ድርጊትን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ማስረጃ አለመቅረቡን ጠቅሶ በነጻ አሰናብቷቸዋል።

ሌሎቹ በክስ መዝገቡ የተካተቱ አጠቃላይ 14 ተከሳሾች ደግሞ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠ ሲሆን÷ ነጻ የተባሉ ተከሳሾችን በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ ከዛሬ ጀምሮ ማረሚያ ቤቱ ከእስር እንዲፈታቸው ታዟል።

ተከላከሉ የተባሉ ተከሳሾችን መከላከያ ማስረጃ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.