በኢትዮጵያ የስታርትአፖች ስነ-ምህዳር ግንባታ ላይ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከጃፓን ዓለም ዓቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ጋር በኢትዮጵያ የስታርትአፖች ስነ-ምህዳር ግንባታ ላይ ለመስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ፈርመዋል።
ዝርዝር ዕቅዱ ላይ የተመከረበት የስምምነት ፕሮጀክቱ በቀጣይ ሦስት ዓመታት የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል።
የፕሮጀክቱ ዓላማ የስታርትአፕ ልማት ስርዓት ከዓለም አቀፉ ጋር የማስተሳሰር ስትራቴጂን ማዘጋጀት፣ ስታርትአፖችን ማፍራትና በዓለም ሀገራት ስራቸውን በማስፋት ከኢንቨስተሮች ጋር መስራት እንዲችሉ ማድረግ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ስታርትአፖች አዳዲስ ምርቶችን በማውጣት፣ አገልግሎትን በማዘመን አዳዲስ ስራዎችንና ሃብትን በመፍጠር የኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ።
ስታርትአፖች በእድገት ሂደታቸው መሰናክሎችና ፈተናዎች ስለሚገጥማቸው ልዩ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግና ስነምህዳሩ የተሳለጠ እንዲሆን የተደረገው ስምምነት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።
የጃይካ ተወካይ አቶ ሳቶሜ ጁን በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱን የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ታንዛኒያ ለማከናወን የሰው ኃይል እና በጀት በመመደብ በቅርቡ ትግበራውን እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
በዚህም ለኢትዮጵያ ስታርትአፖች ዕድገትና መስፋፋት በጃይካ በኩል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ስምምነት ድጋፉን እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።