Fana: At a Speed of Life!

የአዋሽ ወንዝ ላይ የጎርፍ መከላከል ስራ ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለልማት እንዲውል ያስችላል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል በታችኛውና በመካከለኛው አዋሽ የሚከናወነው የጎርፍ መከላከል ስራ ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለልማት እንዲውል እንደሚያስችል የክልሉ የመስኖና ተፋሰስ ቢሮ አስታወቀ።

ባለፉት ዓመታት በክረምት ወቅት በአዋሽ ወንዝ መሙላት ሳቢያ በክልሉ በላይኛውና በታችኛው ተፋሰስ በሚገኙ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ጉዳት ይደርስ እንደነበር ተመላክቷል።

በዚህም በርካታ ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ከማፈናቀል ባለፈ የተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ጉዳት ያስከትል እንደነበር ነው ቢሮ የገለጸው።

የቢሮው ሃላፊ ወልአ ዊቲካ (ኢ/ር) እንዳሉት፥ የአዋሽ ወንዝ ሙላት በተፋሰሱ አካባቢዎች የሚያስከትለውን ጉዳት በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚከናወነው ጎርፍ የመከላከል ስራ በጥሩ ሒደት ላይ ይገኛል።

በመካከለኛው አዋሽ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ በተፋጠነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም በወንዙ ሙላት ችግር ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎች እና የልማት ስራዎች ከስጋት ነጻ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በወንዙ ሙላት ምክንያት ይባክን የነበረን ከ142 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለልማት ማዋል እንደሚቻል ጠቁመዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራው ከአሁኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው ብለዋል።

ፕሮጅክቱን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዘበዋል።

በተፋሰሱ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በበኩላቸው፥ ከዚህ በፊት በክረምት ወቅት ከፍተኛ ስጋታቸው የነበረው የአዋሽ ወንዝ ላይ የጎርፍ መከላከል ስራ በመሰራቱ ስጋታቸውን ተቀርፎ ለልማት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ በላይኛው፣ በመካከለኛውና በታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ የሚያከናውነው የቅድመ ጎርፍ መከላከል ሥራ በቀጣዩ ወር እንደሚጠናቀቅ የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.