Fana: At a Speed of Life!

የወባ በሽታ ስርጭትን በዘላቂነት ለመግታት የከፍተኛ አመራሮች የንቅናቄ መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የወባ በሽታ ስርጭትን በዘላቂነት ለመግታት የከፍተኛ አመራሮች የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል፡፡

መድረኩን ጤና ሚኒስቴር ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዳዛጁት የተገለጸ ሲሆን÷ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ተቋማቱ ከዚህ በፊትም አብረው ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደ ቲቢ እና ኤችአይቪ ያሉ በሽታዎችን መከላከል ላይም በትብብር ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የተለያዩ ወረርሽኞች መከሰታቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም በአየር ንብርት ለውጥ ምክንያት የተስፋፋውን የወባ በሽታ ለመከላከል እና ለማስወገድ በጋራ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ወረርሽኝን መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አንስተው፤ ጤና ሚኒስቴር የወባ ትንኝ ቁጥጥር፣ የማህበረሰብ ግንዛቤ ማሳደግ እና የወባ መድሐኒት ስርጭት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በመከላከል እና በህክምና ስራዎች በበሽታው ምክንያት ይከሰት የነበረውን አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በመከላከያ ሚኒስቴር የጤና መምሪያ ሃላፊ ሌ/ጄነራል ጥጋቡ ይልማ በበኩላቸው÷ ሰራዊቱ ተልእኮውን መወጣት እንዲችል የወባ በሽታን መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሚያደርግ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብጤ መግለጻቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.