በኢንዱስትሪዎች የሚደረጉ ልምምዶች ሰልጣኞች ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንዱስትሪዎች የሚደረጉ ልምምዶች ሰልጣኞች ተጨባጭ እውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ከማድረግ ባሻገር ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ የምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅን ለማስጀመርና የማስፈጸሚያ የህግ ማዕቀፎችን ለማጽደቅ የሚያግዝ መርሐ ግብር ተካሄዷል።
በመርሐ ግብሩ የትስስር ምክር ቤቱ አመራር አካላት፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢዎች፣ የሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ቢሮዎች አመራሮችና አግባብነት ያላቸው ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የትስስር ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በወቅቱ÷ የትምህርት ተቋማት የትስስር አዋጁን በሚፈለገው ፍጥነትና አግባብ በመተግበር ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በኢንዱስትሪዎች የሚደረጉ ልምምዶች ሰልጣኞች ተጨባጭ እውቀትና ክህሎቶችን ይዘው እንዲወጡ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህም ባሻገር ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና የትስስር ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው÷ የምርምርና የትምህርት ተቋማት በትስስሩ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከኢንዱስትሪ ጋር ያላቸውን ቁርኝት በማጠናከር የዘርፉ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ሊሰሩ እንድሚገባ ገልጸዋል።
ትስስሩ በተለይ ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ የሚያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍና በጋራ ለመሥራት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ትምህርት፣ ስልጠናና ምርምርን ማበረታታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት እንደሚያስችልም መግለጻቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ለስኬታማነቱ የከፍተኛ ትምህርት፣ የሥልጠናና የምርምር ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡