የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትውልድ የመገንባት ሚናን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ታሪክ፣ እድገትና ትውልድ የመቅረጽ ጉልህ ሚና የነበረውና ይህን አጠናክሮ እየቀጠለ ያለ ተቋም እንደሆነ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።
ድርጅቱ “ብላቴናት” የተሰኘ ልጆች ላይ የሚያተኩር ባለ 40 ገጽ መጽሔት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ይገኛል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ደራሲያን፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የእድሜውን ያህል አንጋፋና ጥበብ የተሸከመ የታሪክ ማኅደር የሆነ ተቋም ነው።
ተቋሙ ትውልድን የሚጠቅም ሀገር ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተው፤ አሁን ላይ የጀመረው ሥራ ለሀገር የሚመጥን ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ሌሎችም የተቋሙን አርዓያነት በመከተል ቀላል በሆነ መንገድ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተለያዩ ሕትመቶች ለህፃናት ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ላለፉት ስምንት አሥርት ዓመታት ሀገርን ሲገነባና ትውልድ ሲያንጽ መቆየቱን አንስተዋል።
በ83 ዓመት ጉዞው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በየሳምንቱ በልጆች አምድ አስተማሪ ይዘቶች ሲያቀርብ እንደቆየ ተናግረው፤ ሀገር ተረካቢ ህፃናት የሕትመት ሚዲያ እንዲኖራቸው ብላቴናትን ለማሳተም መብቃቱን ተናግረዋል።
መጽሔቱ በትምህርት ቤቶችና በሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት አማካኝነት የሚሰራጭና ከመፅሐፍት አዟሪዎች ማግኘት የሚቻል መሆኑንም ጠቁመዋል።
መጽሔቱ ልጆች እየተዝናኑ እውቀት የሚገበዩበት፣ ስለአገራቸው ወጥ አረዳድ እንዲኖራቸው፣ በስነ-ምግባር እንዲታነፁና አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የይዘት ዝግጅቱ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች፣ በስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎችና ሰዓሊያን የሚሳተፉበትና በቀጣይ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪና የኢፕድ ቦርድ ሰብሳቢ ተወካይ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከዲጂታል ዓለም በተጨማሪ ልጆችን በወረቀት፣ ብራናና ሌሎች የፅህፈት መሳሪያዎች የተፃፉ ጉዳዮችን እንዲያነቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የንባብ ባህልን ለማሳደግ ልጆች በሚውሉበት ስፍራ ፅሁፎችን ማስቀመጥ አስፈላጊ እንደሆነ አንስተው ለዚህም ከወላጆች ጀምሮ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።