Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ በሚጨምሩ አካላት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ይደረጋል – ከንቲባ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ በሚጨምሩና ምርት በሚሰውሩ አካላት ላይ ጠንካራ ቁጥጥርና ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚከናወን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከንግድ ማህበረሰብ አባላትና ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር የፋይናንስ ሚኒስትር ዴዔታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በተገኙበት በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በርካታ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዋነኛነት ዘላቂ ልማትንና አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመገንባት፣ የመንግስትን የእዳ ጫና ለመቀነስና የተረጋጋ ተወዳዳሪ እና የዋጋ ግሽበትን መቀነስ የሚያስችል የገበያ ሁኔታን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡

ተኪ ምርቶችን በማምረትና ለውጪ ገበያ የሚላከውን ምርት በማሳድግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመፍጠር የውጪ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ እድል እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል፡፡

ወቅታዊ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር ዝቅተኛ ገቢ ያለው ማህበረሰብ እንዳይጎዳ የመንግስት ሰራተኞችን ደሞዝ መጨመር፣ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ መደጎም ፣ በተለይም በሴፍቲኔት የታቀፉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ገቢ በሚያስገኝና ተረጂነትን በሚቀንስ መንገድ መደገፍ እንዲሁም የስራ እድልን በስፋት መፍጠርን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚተገበር መሆኑን አውስተዋል፡፡

በቀጣይም ከአምራቾች እና አስመጪዎች ጋር በቅርበት በመስራት እንዲሁም ገበያውን የሚያዛቡ በተለይም ከውጪ ምንዛሪ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ምርቶች ላይ አላግባብ ዋጋ በሚጨምሩ እና ምርት በሚሰውሩ አካላት ላይ ጠንካራ የሆነ ቁጥጥር እና ሕግ የማስከበር ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.