በግብርናው ዘርፍ የሚገኙ ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች የዘርፍን ሽግግር ለማፋጠን ትልቅ ሚና አላቸው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብርናው ዘርፍ የሚገኙ ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች የዘርፍን ሽግግር ለማፋጠን ትልቅ ሚና አላቸው ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር አመራሮች፣ የክልል ስትሪንግ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ዐቢይ ኮሚቴ 2ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ተወያይተዋል።
በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ÷ስራዎችን በዕቅድ መምራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ የሚጠበቅባቸውን ውጤት እንዲያስመዘግቡ በጥራት ከማቀድ ጀምሮ በአግባቡ መምራት የግብርናውን ዘርፍ ሽግግር ለማፋጠን ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ የሚጠበቅባቸውን ውጤት በማስመዝገብ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በመድረኩ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን÷ በዕቅዱ መካተት የሚገባቸውን ጉዳዮች ከተነሱ ሃሳቦች ጋር በማጣጣም ጥሩ አፈፃፀም ለማስመዝገብ በቅንጅት ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡