የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የተሟላ ሀገራዊ ዕድገት እንደሚያመጣ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የተረጋጋ፣ የተሟላና ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ ዕድገት የሚያመጣ መሆኑን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የማማሻሻያ ሂደቱ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ዓለም ባንክን ጨምሮ በዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ የሚተገበር መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ተናግረዋል።
የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉ በገበያው እንዲመራ፣ ዕዳን በማቃለል፣ የገንዘብና ፋይናንስ ፖሊሲ፣ የመንግሥት ገቢና ወጪ ፊስካል ፖሊሲን በማሻሻልና ዕዳን በማቃለል የላቀ ጠቀሜታ አንዳለውም አንስተዋል።
በሪፎርሙ ጫና ለሚደርስባቸው ወገኖች የደሞዝ ጭማሪ አና ድጎማ እንደሚደረግላቸው ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ መዋቅራዊ በሆኑ የአሠራር ግድፈቶች ታንቆ የነበረውን የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት የኢኮኖሚው መሪ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ናቸው፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተረጋጋ፣ የተሟላና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲመዘገብ የሚያደረግ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡