የንግድ ዘርፉን አገልግሎት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ለማገዝ የሚያስችል ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስሰር ሚኒስቴር የዘርፉን አገልግሎት በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዘ ለማድረግ ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና የኤሌክትሮኒክ ንግድ የሚዳብርበትን ስርዓት በማበጀት ተቋሙ ዘርፉን አውቶሜት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህንም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ ይበልጥ ቀላልና ምቹ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አሰራር ነው ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሚኒስቴሩ እየተጠቀመባቸው ባሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማከል የሀገሪቱን የንግድ ስርዓት ለማዘመን በጋራ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
በመረጃ ላይ የተደገፈ ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ማስገንዘባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡